የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ የክልሉን የ2017 በጀት አመት የግማሽ አመት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ከቢሮዎችና ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን ገመገመ፡፡
ጥር 20/2017ዓ.ም
የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ የክልሉን የ2017 በጀት አመት የግማሽ አመት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ከቢሮዎችና ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን ከጥር 20-21/2017 ዓ.ም ገመገመ፡፡
የግምገማ መድረኩን በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት የፕላንና ልማት ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቅነህ በመክፈቻ ንግግራቸው ‹‹ክልላዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሪፓርቱ የተዘጋጀው የሁሉንም ሴክተሮች አፈጻጸም አካቶ ክልላዊ ይዘት እንዲኖረው ተደርጎ ሲሆን መነሻ ያደረገውም ሴክተሮች ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወኗቸውን ተግባራት መሰረት አድርገው አዘጋጅተው ባቀረቡት ሪፓርት ላይ እና የፕላንና ልማት ቢሮ ባካሄደው የአካል ድጋፍና ከትትል ላይ የተገኙ ግኝቶችን አካቶ ነው›› ብለዋል፡፡
ም/ቢሮ ኃላፊው ጨምረውም ‹‹የመድረኩ አላማ የቀረበውን ሪፓርት በአግባቡ በመገምገም እንደ ክልል ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል፤ ድክመቶችን ደግሞ ለይተን አውቀን በማረም በቀጣይ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ የሚያስችል ግብአት ማግኘት ነው›› ያሉ ሲሆን ተሳታፊዎች ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥተው እንዲሳተፉ አሳስበዋል፡፡
የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ ግምገማ ሪፓርቱን ያቀረቡት የፕላን ትግበራ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተዋቸው ፈንታ አንደገለጹት ሪፓርቱ የክልሉ ፈጻሚ ተቋማት በላኩት ሪፓርትና እንዲሁም በዞንና ከተማ አስተዳደሮች በአካል በመገኘት በተደረገ ድጋፍና ክትትል ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው የአፈፃፀም ድክመት የታየባቸውን ተቋማት በቀጣይ ለመደገፍ የሚያስችል ቁመና ያለው ሪፓርት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የግምገማ ሰነዱ የክልሉን ኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ፤ የማህበራዊ ልማት ዘርፍ፤ የመሰረተ ልማት ዘርፍ፤ የህዝብ አገልግሎትና የፍትህና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ፤ እንዲሁም የአካባቢና የአየር ለውጥ ልማት አፈጻሞችን የገመገመ ሲሆን በግምገማው ተቋማቱ የአፈጻጸም ድክመትና ጥንካሬ ተለይቶ በሶስት ደረጃ ማለትም ወደ ፊት የወጡ፤ መካከለኛ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አና ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው በሚል ተለይተዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የክለሉን የ6 ወራት የፕሮጀክቶች ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የኢኮኖሚና ማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች ፕሮጀክት አፈፃፀም ክትትል ባለሙያ በሆኑት በወ/ሮ እመቤት ደሴ ቀርቦ የተገመገመ ሲሆን ሪፖርቱ የፌደራል ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ክትትልን ጨምሮ በገጠር ዘርፍ፤ በከተማ ዘርፍ፤ በማህበራዊ ዘርፍና በአስተዳደር ዘርፍ ስር ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኙና በበጀት አመቱ 17.43 ቢሊዮን ብር የተመደበላቸውን በ34 ተቋማት ስር የሚገኙ 1300 ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ያካተተ ሪፖርት ነው፡፡
የፕሮጀክቶች የፊዚካልና የፋይናንሺያል አፈጻጸም ከተቋም ተቋም የተለያየ ሲሆን በበጀት አመቱ የተመደበላቸውን በጀት ባግባቡ ተጠቅመው በታቀደላቸው ጊዜ ከመፈጸም አንጻር ተቋማቱ ያሉበትን ደረጃ የመለየት ስራ የተሰራ መሆኑን አቅራቢዋ ገልጸዋል፡፡
በግምገማው ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ የክልሉን አጠቃላይ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻጸም ተከታትሎ በአንድ እቅድ አንድ ሪፖርት መርህ መሰረት የክልል ሴክተሮች በጋራ እንዲገመግሙት ማድረጉ መጠናከር የሚገባው አሰራር ነው ተብሏል፡፡
አንደአጠቃላይ የክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈጻጸም ሲታይ ክልሉ በችግር ውስጥ ሆኖም ቢሆን ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በየተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገምግሟል፡፡
Website:-http://anrsbopd.gov.et
No responses yet