የአብክመ ፕላንና ልማት ቢሮ ከኢፌዲሪ ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከክልሉ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አካሄደ፡፡
November 9, 2026
መስከረም 18/2018 ዓ.ም (ፕላንና ልማት ቢሮ) የአብክመ ፕላንና ልማት ቢሮ ከኢፌዲሪ ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "ጠንካራ የመንግስት ኢንቨስትመንት ስርአትና የመረጃ ጥራት ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል ከክልሉ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አካሄዷል፡፡
በውይይቱ ላይ ክቡር ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር)፣ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ፤ የአብክመ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ውይይቱ በመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች አሥተዳደር፣ በዲጂታል የእቅድ ክትትል እና ግምገማ ሥርዓት፣ በክልል የኢኮኖሚ አካውንት እና በአመራር ቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ ያተኮረ ሲሆን፤ ዓላማውም ጠንካራ የመንግሥት ኢንቨስትመንት ሥርዓትን በመዘርጋት እና የመረጃ ጥራትን በማስጠበቅ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ነው።
ክቡር ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ በቴክኖሎጅ የተደገፈ እና ወጥ የሆነ የመረጃ ስርዓት እንዲኖር ለማስቻል ከክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ቢሮ ጋር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ስርአት ለማረጋገጥ መረጃ ማልማትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲዎችን ማውጣት ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁት የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮም እየተሰሩ ያሉ መልካም ስራዎች በቴክኖሎጅ ተደግፈው ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እንደገለፁት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የለማው ፕሮጀክት እንደ ክልል እየተከናወኑ ለሚገኙ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት ወሳኝ ናቸዉ ብለዋል።
በተለይም በፕሮጀክት አስተዳደር ያሉ ተግዳሮቶችን በጊዜ ለማጠናቀቅና እስከታች ያለው መዋቅራችን በመረጃ ላይ የተመሰረተ አመራር ለማረጋገጥና አንድ ጠንካራ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት አስተዋጽኦ የጎላ ነው ሲሉ ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተናግረዋል።
የመረጃ ማልማት ፕሮግራሞች በክልላችን ለመተግበር የክልሉ መንግስት ቁርጠኛ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚጠበቀውን ድጋፍና ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአብክመ ፕላንና ልማት ቢሮ አመራሮችና የማኔጅመንት አባላት ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ጋር በቀጣይ በሚሰሩ ስራዎች ዙሪያ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ፤ቴክኒካል ድጋፍ በሚደረግባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡




