የፕላንና ልማት ቢሮ ከሄልቬታስ አትዮጵያ ጋር በመተባበር በተቀናጀ ማህበረሰብ ተሳትፎ እቅድ ማስፈጸሚያ መመሪያ ዙሪያ የግብአት ማሰባሰቢያ ወርክሾፕ አካሄደ፥
++++
ታህሳስ 7/2018 ዓ.ም – ባህር ዳር – (ፕላንና ልማት ቢሮ)
የአብክመ ፕላንና ልማት ቢሮ የተቀናጀ ማህበረሰብ አሳታፊ እቅድ ለማስፈጸም በተዘጋጀ መመሪያ ዘሪያ ግብአት ለማሰባሰብ ያለመ ወርክሾፕ አካሂዷል።
ወርክሾፑን በንግግር የከፈቱት የፕላንና ልማት ቢሮ ሀላፊ ደመቀ ቦሩ(ዶ/ር) እንደገለጹት “እ.ኤ.አ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ስራ የጀመረው ሄልቬታስ ኢትዮጵያ በክልላችን በሁሉም ዞኖች መዋቅር ፈጥሮ ህብረተሰቡ በጋራ ችግሮቹ ዙሪያ እየመከረ፤ የችግሮቹ መፍቻ እቅድ እያዘጋጀ አካባቢውን እንዲያለማ በማድረጉ በኩል ከፍተኛ ሚና ሲጫወት የነበረ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ በኋላ ግን ድርጅቱ ኮንትራክቱን እየጨረሰ በመሆኑ መንግስት ሃላፊነቱን ወስዶ ልማቱን በህብረተሰብ ተሳትፎ የማስቀጠል ግዴታ አለበት፤ይህን ሀላፊነትን ለመወጣት ተሳትፎውን የሚመራበት መመሪያ ያስፈልጋል” ብለዋል።
ቢሮ ሀላፊው የወርክሾፑን አላማ ሲገልጹ “የክልሉን የሃያ አምስት አመት አሻጋሪ እድገትና ዘላቂ ልማት ፍኖተ ካርታ እና የአምስት አመቱን አሻጋሪ እድገትና ዘላቂ ልማት እቅድ ለማስፈጸም የተቀናጀ የማህበረሰብ አቀፍ ተሳትፎን በስርአት መምራት አስፈላጊ በመሆኑ ፕላንና ልማት ቢሮ ላዘጋጀው በቀበሌ ደረጃ የማህበረሰብ አሳታፊ እቅድ ማስፈጸሚያ መመሪያ ግብአት የሚሆን ሃሳብ ለማሰባሰብ የተዘጋጀ ወርክሾፕ ነው” ብለዋል።
ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት ሀላፊዎችና ተወካዮች በወርክሾፑ የተገኙ ሲሆን መመሪያውን ለማዳበር ይረዳሉ ያሉትን ሀሳብና አስተያየት አቅርበዋል።
ማህበረሰቡ የልማት ችግሮቹን በጋራ ውይይት ለይቶ፤ በቅደም ተከተል አስቀምጦ ችግሮቹን የሚቀርፍበትና ልማት የሚያመጣበት እቅድ ለማዘጋጀትና ለመፈጸም የሚያስችለው የአፈጻጸም መመሪያ የሚያስፈልገው መሆኑን በውይይታቸው የገለጹ ሲሆን ለዚህም ፕላንና ልማት ቢሮ ያዘጋጀው መመሪያ ጸድቆ ስራ ላይ መዋል አለበት ብለዋል።
“የክልሉ መንግስት ያዘጋጀው አሻጋሪ እድገትና ዘላቂ ልማት እቅድ ውጤታማ ሆኖ እንዲፈጸምና የታሰበው ብልጽግና እንዲረጋገጥ የህብረተሰቡን ተሳትፎ በአሰራር በመምራት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ማድረግ ይገባል” ሲሉ የወርክሾፑ ተሳታፊወች ጨምረው ገልጸዋል።
Researching, innovating, influencing”
Website:-http://anrsbopd.gov.et
Telegram:-https://t.me/planpdb2014
Facebook:- https://www.facebook.com/profile.php?id=61576561109939
YouTube channel: – https://www.youtube.com/@ANRSBOPD-2014
Instagram :- https://www.instagram.com/plan_and_development_bureau/
x-account:- https://x.com/logout
tiktok:- https://www.tiktok.com/@anrs_plan_and_developmen?lang=en-GB
gmail address:- plananddevelopmentbureau@gmail.com

No responses yet